Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ መከላከያ ሀይሎች የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 25 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ታንዛኒያ ገብተዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ታንዛኒያ ሲደርሱ የታንዛኒያ መከላከያ ሃይል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ጃኮብ ማኩንዳ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የጉብኝቱ ዓላማ የሁለቱ እህትማማች ሀገራት የመከላከያ ሀይሎች ግንኙነትና ትብብርን እንዲሁም ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ በሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ያለመ መሆኑን የመከላከያ ሰራዊት ገጽ መረጃ ያመላክታል።

የሁለቱ ሀገራት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች በሁለቱ የፖን አፍሪካኒዝም እህትማማች ሀገሮች መከላከያ ሃይል የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በማዋሊሙ ጁሊየስ ኔሬሬ እና በአፄ ሃይለ ስላሴ የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትና ትብብር አሁን ላይም ተሞክሮዎችን በመለዋወጥና በትብብር መሥራት እንደቀጠለ መሆኑን በዚህ ወቅት ገልፀዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ታንዛኒያ በዓለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች እንዲሁም በአባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ በተፋሰሱ ሀገሮች ስምምነት መሠረት እያሣየች ያለውን መልካም ትብብርም አድንቀዋል።

በተጨማሪም ታንዛኒያ ኢትዮጵያ በውስጧ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት በመደገፏ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ምስጋና አቅርበዋል።

የአሁኑ የኢትዮጵያ እና የታንዛኒያ ወታደራዊ አመራሮች ግንኙነት የሁለቱን ፖን አፍሪካኒዝም እህትማማች ሀገሮች የቀጣይ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክረው መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም በሁለቱ ሀገሮች የመከላከያ ሀይሎች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በወታደራዊ አቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ በወታደራዊ ቴክኖሎጅ ሽግግር መስክ ያለውን ትብብር በሚቀጥሉት ዓመታት ማሣደግ እንዳለባቸውም ስምምነት ደርሰዋል።

የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በታንዛኒያው ህዝባዊ መከላከያ ሃይል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ጃኮብ ማኩንዳ ታንዛኒያን እንዲጎበኙ በመጋበዛቸው በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Exit mobile version