የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የቤጂንግ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት ዩኒቨርሲቲ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

By Amele Demsew

December 05, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 25 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የቤጂንግ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ።

ሁለቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፈረንጆቹ 2020 መሰጠት የጀመረውን የአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራም በመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር በድጋሚ ለማስቀጠል ሥምምነት ደርሰዋል።

ሥምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና የቤጂንግ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት ዩኒቨርሲቱ ፕሬዚዳንት ያንግ ዳን (ፕ/ር) መፈረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የዛሬው ሥምምነት የሁለቱን ሀገራት ቋንቋዎች ጥናት በየተቋማቱ መስጠትን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

በያንግ ዳን (ፕ/ር) የተመራ የቤጂንግ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት ዩኒቨርሲቲ የተመራ ልዑክ በትናንትናው ዕለት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መወያየቱ ይታወሳል።

አቶ ደመቀ መኮንን ባለፈው ግንቦት ወር በዩኒቨርሲቲው ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፥ በወቅቱ መሰል ውጥኖች የሃገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ጠቃሚ እንደሆኑ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።