Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

35 አምቡላንሶችና 120 ሞተር ሳይክሎች በግጭት ለተጎዱ ክልሎች ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስቴር የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት 35 አምቡላንሶችንና 120 ሞተር ሳይክሎች በግጭት ለተጎዱ ክልሎች አስረክቧል፡፡

በዓለም ባንክና በመንግስት መካከል በተደረገ ስምምነት በሚኒስቴሩ የተቋቋመው ፕሮጀክት ነው በኢትዮጵያ በአራት ክልሎች በተለያዩ ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማትን ለማገዝ የሚውሉ 35 አምቡላንሶችንና 120 ሞተር ሳይክሎችን ዛሬ ለክልሎቹ ያስረከበው፡፡

ድጋፉ የተደረገላቸው በአፋር፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው 35 ወረዳዎች ናቸው ተብሏል፡፡

በርክክቡ ወቅት እንደተገለፀው÷ከተደረገው የተሸከርካሪዎች ድጋፍ በተጨማሪ በጤናው ዘርፍ የመድሐኒቶች እና የተለያዩ የጤና መገልገያ ቁሳቁሶች በፕሮጀክቱ አማካኝነት በግዥ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡

በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት አማካኝነት በትምህርት ዘርፍ 56 ሺህ 577 የመማሪያ ወንበሮች ተሰራጭተዋልም መባሉን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም ከታቀዱት ተግባራት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችን የኤሌክትሮኒክ መፅሃፍትና ሌሎች የትምህርት መርጃዎች ተጠቃሚ የማድረግ ስራ መከናወኑም ተገልጿል፡፡

ተመሳሳይ ድጋፍ በግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው የትግራይ ወረዳዎች የተደረገ ሲሆን÷ ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ ምክንያት በሶስተኛ ወገን አማካኝነት ፕሮጀክቱ ሲተገበር ቆይቶ የተጠናቀቁ ስራዎችን የማስረከብ ስራዎች አየተሰሩ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

Exit mobile version