አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሙስና ክስ ዳግም መታየት መጀመሩ ተገልጿል፡፡
በፈረንጆቹ ጥቅምት 7 የተፈፀመውን ክስተት ተከትሎ ከእስራኤል የፍትህ ሚኒስትር በተሰጠ አስቸኳይ ትዕዛዝ ጉዳዩ ባለበት እንዲቆይ መደረጉ የሚታወስ ነው።
በእየሩሳሌም የሚገኘው ፍርድ ቤት ኔታንያሁ በተከሰሱባቸው በርካታ የሙስና ወንጀሎች ላይ ያተኮረውን ጉዳይ ከዛሬ ጀምሮ ማየት እንደሚጀምር የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ኔታንያሁ በ2019 በቀረቡባቸው 1000፣ 2000 እና 4000 በመባል በሚታወቁት በማጭበርበር፣ ጉቦ እና በእምነት ማጉደል ሦስት ክሶች እንደቀረቡበቸው ይታወቃል።
በክስ 1000 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለቤታቸው ሳራ ጋር በመሆን ከታዋቂው የሆሊውድ ፕሮዲዩሰር አርኖን ሚልቻን እና አውስትራሊያዊው ቢሊየነር ነጋዴ ጄምስ ፓከር ጋር ለፖለቲካ ጥቅም ሲሉ ሻምፓኝ እና ሲጋራዎችን ጨምሮ ስጦታዎችን ተቀብለዋል በሚል ተከሰዋል።
የጉቦ ክስ በሀገሪቱ ህግ መሰረት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን ማጭበርበር እና እምነትን ማጉደል ደግሞ እስከ ሶስት ዓመት እስራት ያስቀጣል።
ይሁንና እስራኤልን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ምንም ዓይነት ጥፋት አልፈጸምኩም ሲሉ ማስተባበላቸው ተገልጿል።
ችሎቱ በግንቦት 2020 የተጀመረ ሲሆን በመከላከያ ምስክር እና በዐቃቤ ህግ ክርክር እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተደጋጋሚ መስተጓጎሉን አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኔታንያሁ ህግ አውጪውን አካል ተጠቅመው ህጋዊ ችግሮቻቸውን ለማምለጥ ሞክረዋል ተብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ባቀዱት አወዛጋቢ ዕቅድ እስራኤላውያን ለወራት በዘለቀ የተቃውሞ ሰልፎች እንደቆዩ ዘገባው አስታውሷል።
የማሻሻያ ዕቅዱን ተከትሎ ተቺዎች የታቀዱት ለውጦች የፍትህ ስርዓቱን ፖለቲካዊ የሚያደርጉ፣ የፍትህ ነፃነቱን የሚያበላሹ፣ ሙስናን የሚያዳብሩ እና ኢኮኖሚ የሚጎዱ ናቸው በሚል ወቀሳ አቅርበዋል።
ይሁን እንጅ ኔታንያሁ የማሻሻያ ዕቅዱ በሶስቱ የመንግስት አካላት መካከል ያለውን ትክክለኛ ሚዛን ለመመለስ ያለመ መሆኑን በመግለፅ ተቃውሞውን ውድቅ አድርገዋል።