ዓለምአቀፋዊ ዜና

የእስራዔል ጦር ወደ ደቡባዊ ጋዛ እየገፋ መሆኑ ተሠማ

By Alemayehu Geremew

December 04, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራዔል ምድር ጦር ወደ ደቡባዊ ጋዛ እየገፋ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ወታደራዊ ኃይሉ የሃማስን ማዕከላዊ ዕዞች ፣ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ሥፍራዎች እንዲሁም የባሕር ኃይሎቹን ዒላማ አድርጎ እየገፋ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ከሃማስ ጋር የተደረሰው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሥምምነት ባለፈው አርብ ማብቃቱን ተከትሎ እስራዔል በአዲስ መልክ ጥቃት መክፈቷ ይታወሳል።

በጉዳዩ ላይ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን÷ እስራዔል ራሷን የመከላከል መብት ቢኖራትም ለንፁሐን ደኅንነት መጠንቀቅ እንዳለባት አሳስበዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ሁኔታው “ከጥፋትም በላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስም ÷ እጅግ በጣም በርካታ ፍልስጤማውያን እንደተገደሉ ነው የተናገሩት።

አንድ ሥማቸው ያልተገለጸ የእስራዔል ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ፥ በመሃል ንፁሐን እንዳይጎዱ እስራዔል የምትችለውን ሁሉ እያደረገች ነው ማለታቸውን የዜና ምንጩ አስነብቧል፡፡

በእስራዔል ሃማስ ጦርነት እስካሁን 6 ሺህ ህጻናትን ጨምሮ ከ15 ሺህ 500 በላይ ፍልስጤማውያን ለህልፈት መዳረጋቸውን የጤና ተቋማት ምንጮችን ዋቢ ያደረገው የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።