የሀገር ውስጥ ዜና

የፋብሪካዎች የድንጋይ ከሰል ፍላጎት 80 በመቶውን በሀገር ውስጥ ማሟላት መቻሉ ተነገረ

By Shambel Mihret

December 04, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋብሪካዎች የድንጋይ ከሰል ፍላጎት 80 በመቶ የሚሆነው በሀገር ውስጥ ማሟላት መቻሉን የማዕድን ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የድንጋይ ከሰል ምርቱን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማሟላት እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አሥፈፃሚ አቶ አወቀ ተሥፋው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፤ በርካታ የድንጋይ ከሰል አምራቾች በሀገር ውሥጥ አሉ።

አምራቾቹ በተለይ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ትሥሥር እንዲፈጥሩ በማድረግ ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ግብዓት በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የድንጋይ ከሰል ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ማሟላት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለ አንስተው፤ ምርቱን ሙሉ በሙሉ ለመተካት እየተሠራ ያለው ሥራ የውጭ ምንዛሬ ወጪን እንደሚያድን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በሠሎሞን ይታየው