የሀገር ውስጥ ዜና

በምስራቅ አፍሪካ ግዙፉ የንፋስ ሀይል ማመንጫ በሶማሌ ክልል ሊገነባ ነው

By Shambel Mihret

December 03, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 600 ሚሊየን ዶላር ወጭ የሚደረግበት 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የንፋስ ሀይል ማመንጫ በሶማሌ ክልል ሊገነባ ነው፡፡

ይህንን እውን ለማድረግ የገንዘብ ሚኒስቴር ከአሜአ ፓወር ኩባንያ ጋር የስምምነት ፊርማ ተፈራርሟል፡፡

በሶማሌ ክልል አይሻ አካባቢ የሚገነባው የንፋስ ሀይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት የሚችል ነው ተብሏል፡፡

አጠቃላይ የንፋስ ሀይል ማመንጫው 600 ሚሊየን ዶላር ወጭ የሚደረግበት ሲሆን÷ አሜአ ፓወር በተሰኘ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኩባንያ እንደሚሰራ ተጠቅሷል፡፡

ስምምነቱ በመንግስትና በግል አልሚዎች ማእቀፍ የሚሰራ ትልቁ ኢንቨስትመንት እንደሚሆን እንዲሁም በንፋስ ሀይል ማመንጫ ከምስራቅ አፍሪካ ግዝፉ ይሆናል መባሉን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል ላይ መሰረት ላደረገ የሀይል አቅርቦት ስትራቴጂዋም ስምምነቱ ተጨማሪ ግብአት ይሆናል ነው የተባለው፡፡