የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አሳለፈ

By Mikias Ayele

December 02, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ካቢኔ ዛሬ 3ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በስብሰባውም÷ በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ እና አገልግሎትን በማሳለጥ ጉልህ ድርሻ በሚኖራቸው የተቋማት መዋቅር ማሻሻያ ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በዚህም÷ የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ዓለም አቀፍ ደረጃውን እንዲጠብቅ እንዲሁም በየጊዜው የሚጨምረውን የተጠቃሚዎች ፍላጎት ለማሟላት የ24 ሠዓት አገልግሎት እንዲሠጥ ረቂቁ ፀድቋል፡፡

በተጨማሪም ቁጥር 2 የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት በመገናኛ አካባቢ እንዲገነባ መወሰኑን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል÷ ካቢኔው ለተገልጋይ እርካታ ጉልህ ድርሻ ያላቸውን ተቋማት በጥናት መዋቅራዊ ሪፎርም ለማድረግና በማዘመን ለኅብረተሰቡ ተገቢ አገልግሎት እንዲሠጡ ለማስቻል የቀረበውን ረቂቅ ደንብ መርምሮ አጽድቋል።

ሪፎርሙን ለመተግበር የሚያስቸግሩ እና የተስተዋሉ የሥራ ፍሰት ችግሮች፣ የሥራ ድግግሞሽና ተግባራት ፍሰት መቆራረጥ፣ የስታንዳርድ ክፍተቶች ፣ የሥነ-ምግባር፣ የሰብዕና ችግሮችን፣ የባለሙያና ሙያ ስብጥር ክፍተቶችን እንዲሁም የመዋቅራዊ ይዘት ጉድለቶች በጥናት እንደሚለዩ ተገልጿል፡፡