አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 21 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስኬት የሚለካው በድርጊት እንጂ በሚወሰኑ ውሳኔዎች አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዱባይ እየተካሄደ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ብክለትን ከመከላከል አንጻር ያዘጋጀቸውን ሃገር በቀል መፍትሄም በመድረኩ አንስተዋል።
በዚህም ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ተግባራዊ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።
ባለፉት አምስት አመታትም 130 ሺህ ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች መቋቋማቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በየአመቱም በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ችግኝ በማፍላት፣ በመትከልና በመንከባከብ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለማህበረ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች የምንሰጠውን ምላሽ ይወክላልም ነው ያሉት።
ይህ መርሐ ግብርም የካርበን ልቀትን ለመቀነስ፣ ሥነ ምህዳርን ለመጠበቅ እና የሥራ እድልን በመፍጠር እንደ ቱሪዘም ያሉ ዘርፎችን ለማነቃቃት ይረዳልም ብለዋል ።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 32 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ መትከሏን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በፈረንጆቹ 2026 ደግሞ 15 ቢሊየን ችግኝ የመትከል ሀገራዊ እቅድ መኖሩንም ነው የገለጹት።
ይህ ሲጠናቀቅም መርሐ ግብሩ ዓለም ላይ ትልቁ የደን ልማት ፕሮጀክት እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ይህን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሯን ለጎረቤት ሀገራት ማጋራቷን በማንሳትም ይህም በአፍሪካ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ነው የተናገሩት።
70 በመቶ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ካለባት ሀገር እንደመጡ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለመጪው ትውልድ እንዴት የተሻለች ዓለም ማውረስ እንደሚችሉ ማሰብ እንቅልፍ እንደሚነሳቸው ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም የፖለቲካ ጉዳይ ከሆነ ከሶስት አስርት አመታት በላይ አስቆጥሯል ሲሉም አመላክተዋል።
ስምምነቶች ተደርሰዋል፣ የአየር ንብረት አጀንዳን ከማህበራዊ ፣ፖለቲካዊ ፣ ዘላቂ ልማት እና ምጣኔ ሀብታዊ ገጽታዎች ጋር በማጣመር ጥሩ እመርታ አሳይተናልም ብለዋል።
ነገር ግን በዓለም አቀፍ የስቶክ ቴክኖሎጂ ስር ተግባሩ ሲገመገም እንደሚያሳየው የዓለም ሙቀትን ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴሊሺየስ በታች ለማድረግ ከተያዘው ዓላማ በጣም የራቀ እንደሆነ አንስተዋል።
ይህ በጣም በተጎዱ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ውጤት ለሚያስገኝ ተግባር መነቃቃት እንደሚያስፈልግና ስኬት የሚለካው በድርጊት ብቻ እንጂ በሚወሰኑ ውሳኔዎች አለመሆኑንም አስገንዝበዋል።
አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ጠንካራ አጋር መሆኗን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ አረንጓዴ – ግዙፍ ጦርነቶችን ለመዋጋት ጥረት ላይ መሆኗንም አመላክተዋል።
ይሁን እንጂ አህጉሪቱ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ አስተዋጽኦ ብታበረክትም ለአየር ንብረት ተጽእኖ በጣም ተጋላጭ ናት ሲሉ አክለዋል።
ተደጋጋሚ ድርቅ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የእንስሳት ሞት በህዝቡ ህይወትና ኑሮ ላይ ካደረሱት በርካታ የአየር ንብረት አደጋዎች መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
ምድራችንን ለመጠበቅ እና ለመፈወስ የሚደረገው ትግል ለኢትዮጵያ የእድገት እና የብልጽግና ጦርነት ነው በማለትም ገልጸውታል።