የሀገር ውስጥ ዜና

የ“መደመር ትውልድ” መፅሐፍ በፓኪስታናውያን ዘንድ ዝናው እየጨመረ መሆኑ ተነገረ

By Alemayehu Geremew

December 01, 2023

አዲስ አበባ፣ ኅዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “የመደመር ትውልድ” የተሠኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእንግሊዝኛው ትርጉም መፅሐፍ በመላው ፓኪስታናውያን ዘንድ ዝናን እያተረፈ መሆኑ ተነገረ፡፡

“የመደመር ትውልድ” የተሠኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 3ኛ መፅሐፍ ፍልስፍና በፓኪስታን ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን እና ተነባቢነትን እያገኘ መምጣቱን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

መፅሐፉ በኢትዮጵያ ዕውን እየሆነ ስላለው ጠንካራ የምጣኔ ሐብት ዕድገት እና ቀጣይ የልማት አቅጣጫ በሠፊው ያትታል፡፡

በፓኪስታን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የመደመር ትውልድ የተሠኘውን መፅሐፍ በሀገሪቷ ማስተዋወቁ ይታወሳል፡፡

በዛሬው ዕለትም በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ጀማል በከር አብዱላ ይህን “የመደመር ትውልድ” መፅሐፍ ኢትዮጵያ ስለተያያዘችው የልማት አቅጣጫ በቅርበት ለሚከታተሉት ፓኪስታናዊ ነጋዴ እና በጎ አድራጊ አዛም ኢፈንዲ አበርክተዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይም በኢትዮጵያ በንግዱ ዘርፍ መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከራቸው ተገልጿል፡፡