የሀገር ውስጥ ዜና

18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በተለያዩ ክልሎች እየተከበረ ነው

By Amele Demsew

December 01, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 21 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በተለያዩ ክልሎች በክልል ደረጃ በመከበር ላይ ይገኛል ፡፡

በሐረሪ ክልል በክልል ደረጃ 18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል እየተከበረ ነው።

በዓሉ “ብዝሓነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ነው እየተከበረ የሚገኘው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ የወል ማንነቶችን በማጠናከር ከሁላችንም ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ለመገንባት መስራት ይገባል።

ፍፁም ልዩነትና ፍፁም አንድነት የሚል አስተሳሰቦች እንደ ሀገር ኢትዮጵያን ሊያፀና እንደማይችልም ነው የጠቆሙት።

የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱልሰላም በበኩላቸው፥ የዘንድሮው በዓል በአጓራባች ሶማሌ ክልል መከበሩ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

በዓሉን ለማክበር ወደ ጅግጅጋ ለሚያቀኑ እንግዶች ከሕዳር 23 ቀን ጀምሮ በሐረር ከተማ አቀባበል ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመላክተዋል።

በበዓሉ ከአጓራባች የድሬዳዋ አስተዳደርና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በተመሳሳይ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን ካራት ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

በመድረኩ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አዳማ ትምጳዬ ጨምሮ ሌሎች የክልልና የዞን አመራሮች፣ የብሔር ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መታደማቸውን የክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

በእዮናዳብ አንዷለም ፤ ተጨማሪ መረጃ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ