የሀገር ውስጥ ዜና

ለኢትዮጵያ ሰላም መረጋገጥ የህዝቦች የነቃ ተሳትፎና የፀጥታ ሃይሉ ቅንጅት ወሳኝ ነው -ሌ/ ጄ ሹማ አብደታ

By Amele Demsew

November 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ ሰላም መረጋገጥ የህዝቦች የነቃ ተሳትፎና የፀጥታ ሃይሉ ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ እና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ዋና ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ገለጹ፡፡

ሌ/ ጄ ሹማ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ከሚሴ ከተማ ከዞን፣ ከወረዳ እና ከአራት ከተማ አስተዳደሮች እና ከፀጥታ ሃይል አማራሮች እንዲሁም ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በአከባቢው የሰላምና የፀጥታ ዙሪያ ተወያይተዋል።

በመድረኩም የዞኑ ህዝብ ለሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት አስፈላጊውን መስዋዕትነት እየከፈለ መቆየቱን አስታውሰው÷ዛሬም በአካባቢው ሲንቀሳቀስ የነበረውን አሸባሪው ሸኔን ለመመንጠር እያደረገ ላለው አስተዋፅኦ አመስግነዋል፡፡

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ አሊ በበኩላቸው÷ አሸባሪው ሸኔን ከመዋጋት አንፃር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት 108 የሸኔ አባላት እጃቸውን ሰጥተው ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሰዋል ማለታቸውንም የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሰራዊቱ እና ሌሎች የዞኑ የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ስምሪት 162 የሸኔ ሴሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና በርካቶች መደምሰሳቸውንም ገልፀዋል፡፡