ዓለምአቀፋዊ ዜና

የኮፕ28 ፕሬዚዳንት ኢንዱስትሪዎች ታዳሽ ኃይል ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ

By Meseret Awoke

November 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮፕ28 ፕሬዚዳንት ሱልጣን አል ጃብር (ዶ/ር) ኢንዱስትሪዎች ታዳሽ ኃይል ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በኮፕ28 ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ኢንዱስትሪዎች በታዳሽ ቴክኖሎጂ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ እንዲዘምኑ እና መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ አሳስበዋል።

ከረጅም ውይይት በኋላ የነዳጅ ኩባንያዎች በፈረንጆች 2023 ለመጀመሪያ ጊዜ የምድር የአየር ንብረትን ከሚያዛባው የሚቴን ልቀት ዜሮ ለማድረስ ቁርጠኛ እንደሆኑ ማረጋገጣቸውን አንስተዋል፡፡

አሁን ብዙ የነዳጅ ኩባንያዎች ዜሮ 2050 ግብን በመቀላቀል ለመጀመሪያ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር ጉዞ መጀመራቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ሀገራት የቀጣይ ዙር ሀገራዊ ግቦቻቸው አካል በመሆን የካርበንዳይ ኦክሳይድ ልቀትን ዜሮ ለማስገባት ዝግጅት እንዲያደርጉ ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ፕሬዚዳንቱ በከባድ ትራንስፖርት፣ በብረት፣ ሲሚንቶ እና አሉሚኒየም ምርት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች የካርቦን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት እንዲፋጠን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጉባኤውን ውጤት ወደ መሬት በማውረድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው ÷ በዚህም “ብዙዎች በጉዳዩ ላይ ያጠፉትን እምነት እንመልስ” ሲሉ ተናግረዋል።

በአየር ንብረት አጀንዳ ውስጥ ዋነኛው የስኬት ጉዳይ ገንዘብ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ ፥ “የፋይናንስ ክፍተቱን በማስተካከል ለዓለምአቀፉ ግብ በጠንካራ ማዕቀፍ ላይ መስማማት አለብን” ብለዋል።

‘’ተፈጥሮን፣ ሕይወትን አንዲሁም መተዳደሪያን የእቅዶቻችን ቁልፍ ተግባር እናድርግ” ሲሉም አሳስበዋል፡፡

#COP28 #UN #Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!