Fana: At a Speed of Life!

በህንድ ዋሻ የተናደባቸው ሠራተኞች ከ17 ቀናት በኋላ በሕይወት መውጣታቸው ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በህንድ ዋሻ የተናደባቸው ሠራተኞች ከ17 ቀናት በኋላ በሕይወት በመውጣታቸው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ መልዕክት አስተላለፉ።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 17 ቀናት ከዘለቀው የነፍስ አድን ከባድ ጥረት በኋላ ከተናደው ዋሻ ውስጥ በትናንትናው ዕለት የወጡ ሰራተኞችን በስልክ አነጋግረዋል።
 
በህንድ ኡታራክሃንድ ግዛት ባለው ዋሻ ውስጥ በፈረንጆቹ ሕዳር 12 በደረሰው ናዳ እዛው የቀሩትን 41 ሰዎች ለማትረፍ የነፍስ አድን ሠራተኞች ከስድስት ሰዓታት በላይ እንደፈጀባቸው ተገልጿል፡፡
 
ከሠራተኞቹ መካከል ሴባ አህመድ የተባለው ሰው ከተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች የመጡ 41 ሰዎች እንደነበሩና ሁሉም እንደወንድም እንደነበሩ ተናግሯል፡፡
 
ሰራተኛው በተጨማሪም በዋሻው ውስጥ የእግር ጉዞ ያደርጉ እንደነበር እና ጠዋት ላይም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ይህም በአካል ብቃት ጠንካራ ሆነው እንዲቆዩ እንደረዳቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግሯል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በበኩላቸው ሰራተኞቹን በህይወት በመትረፋቸው እንኳን ደስ አላችሁ ያሉ ሲሆን ላዩት ፅናትና ትዕግስትም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
 

ሠራተኞቹ 90 ሴንቲ ሜትር ስፋት ባለው የብረት ቱቦ በኩል በተሽከርካሪ አልጋ ተስበው የወጡ ሲሆን አጠቃላይ ሂደቱም አንድ ሰዓት መፍጀቱ ተመላክቷል፡፡

 
ከዋሻው የወጡት ሰራተኞች በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው በሚገኝ የህክምና ተቋም ውስጥ እንደሚገኙ እና ዶክተሮች ደህንነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ወደ ትውልድ ግዛታቸው ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዲዲ ኒውስ ዘግቧል።
 
የቻር ዳም አውራ ጎዳና አካል የሆነው ዋሻው ከጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን አራት የሂንዱ የሐጅ ጉዞ ጣቢያዎችን በ890 ኪሎ ሜትር የመንገድ አውታር ለማገናኘት ያለመ መሆኑም ተመላክቷል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.