አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ በላቦራቶሪ ምርምራ ተገኝቶባት በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የለይቶ ህክምና ማዕከል ውስጥ ክትትል እየተደረገላት የምትገኘው የ34 ዓመት እናት 3 ነጥብ 1 ኪሎ ግራም የሚመዝን ወንድ ልጅ በቀዶ ህክምና በሰላም ተገላግላለች።
ከህጻኑ በተወሰደው ናሙና በተካሄደው የላቦራቶሪ ምርመራ ቫይረሱ እንደሌለበት ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን እናቱም በጽኑ ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላት ይገኛል።
የጤና ሚኒስቴርም የዶ ህክምናውን በተሳካ ሁኔታ ላከናወኑ የህክምና ቡድን፣ ካጠገባቸው ሳይለዩ የህክምና ክትትል ለሚያደርጉላቸው እና በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ከጎናቸው ለነበሩ እንዲሁም በቆራጥነት እያገለገሉ ለሚገኙ ለሁሉም የህክምና ባለሙያዎች እና የድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ምስጋና አቅርቧል።
የኮቪድ19 ወረርሽኝ እስካሁን ባለው መረጃ በእርግዝና ወቅት ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድሉ በጣም አነስተኛ ነው።
ነገር ግን አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በተወሰኑ ህጻናት ላይ በእርግዝና ወቅት፣ በምጥ ወይም ከምጥ በኋላ እንደሆነ ባይረጋገጥም ለህጻናቱ በተደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ያሳያሉ።
ምንም እንኳ በእርግዝና እና ወሊድ ወቅት ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም ከወሊድ በኋላ በጡት ማጥባት ወቅት እና ዘወትር በሚኖር ንክኪ ቫይረሱ የመተላለፍ እድሉ ከፍተኛ ስለሆነ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመከራልም ነው ያለው ሚኒስቴሩ።
ጥንቃቄዎቹ ጡት ከማጥባት ወይም ማንኛውም ንክኪ ከማድረግዎ በፊት እና በኋላ እጅዎትን በሳሙና እና በውሃ መታጠብ፣ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ የሚኖሩበትን ክፍል በቂ አየር እንዲኖረው እና እንዲናፈስ ማድረግ፣ ለክትባት የሚኖራቸውን ቀጠሮ በአግባቡ መከታተል፣ በቂ የፀሀይ ብርሀን እንዲያገኙ ማድረግ፣ የተለያዩ በሽታዎች ምልክትን ማወቅ እና የህጻናትን ጤና ማስተዋል ይኖርባቸዋልም ብሏል።
በዚህ አጋጣሚ እናቶች በእርግዝና ወቅት ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ የመከላከያ መንገዶችን አጥብቀው መተግበር፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ በቂ እረፍትን መውሰድ፣ የእርግዝና ክትትል ማድረግ እንዲሁም በጤና ተቋማት መውለድ እጅግ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ምክር በአግባቡ እንዲተገብሩም አሳስቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።