አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ለ6 የአፍሪካ ሀገራት ቃል የገባችውን የነፃ የእህል እና የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ ከቀናት በኋላ ማቅረብ እንደምትጀምር አስታውቃለቸ፡፡
ድጋፉ ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለእህል እና አፈር ማዳበሪያ እጥረት ተጋላጭ የሆኑ ሀገራትን ለመደገፍ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ዚምባቡዌ እና ማሊ የሩሲያ የነፃ የእህል እና የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሀገራት ሲሆኑ ሶማሊያ እና ቡርኪናፋሶ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሀገራት ናቸው ተብሏል፡፡
የሩሲያ ግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ ሩሲያ ቃል በገባችው መሰረት በየአመቱ 200 ሺህ ቶን የእህል እና የአፈር ማዳበሪያ ለሀገራቱ ታቀርባለች።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ሀምሌ ወር በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ስብሰባ ላይ ለስድስት የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የእህል እና የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡
ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥን ከማሳደግ በተጨማሪ ለአፍሪካ ሰላም የበኩሏን እየተወጣች መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተከሰተው ጦርነት በአለም የሸቀጦች አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ የተፈጠረ ሲሆን የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ የችግሩ የመጀመሪያ ተጎጂ ሆነው መቆየታቸውን ኒው ዚምባቡዌ ዘግቧል፡፡