የሀገር ውስጥ ዜና

በሙስና የተመዘበረ 9 ቢሊየን ብር ማስመለስ መቻሉ ተገለጸ

By Melaku Gedif

November 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሙስና ወንጀልን በመከላከል ሒደት 9 ቢሊየን ብርና ከ4 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ማስመለስ መቻሉን የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተቋቋመው የሙስና መከላከል ግብረ ኃይል አሁን ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያሳዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የኮሚሽኑ ም/ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው÷ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ተጋላጭ ዘርፎችን በመለየት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

የመሬት፣ የግዥና ንብረት እንዲሁም የኮንትራት አስተዳደሮችና የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ለሙስና ተጋላጭ መሆናቸው በጥናት መለየቱንም አስረድተዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የተቋማትን የሙስና ተጋላጭነት በማጥናትና ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተደራሽ በማድረግ ብልሹ አሰራርንና ሌብነትን ለማስቀረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ በዋናነት ሙስናን ለመከላከል በቅንጅት ባከናወናቸው ተግባራት 9 ቢሊየን የሚጠጋ ጥሬ ብርና ከ4 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

መንግስት በመላ ሀገሪቱ ሙስናን ለመከላከል ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡