አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 15 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዳጋስካር ምርጫ ፕሬዚዳንት አንድሪ ራጆኤሊና ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታወቀ።
በምርጫው ፕሬዚዳንቱ 59 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውም ነው የተገለጸው።
በምርጫው የቅርብ ተቀናቃኞቻቸው የሆኑትን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ማርክ ራቫሎማናና እና ሲቴኒ ራንድሪያናሶሎኒያኮን በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋልም ነው የተባለው።
ይሁን እንጅ ተፎካካሪዎቻቸው ውጤቱን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።
ውጤቱ ይጸና ዘንድም የማዳጋስካር ሕገ- መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የኮሚሽኑን የምርጫ ውጤት በዘጠኝ ቀናት ውስጥ ማጽደቅ ይኖርበታል።
በምርጫው ተሳታፊ የነበሩ ዕጩ ተወዳዳሪዎችም መራጮች ድምጽ እንዳይሰጡ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር ተብሏል፡፡
ይህን ተከትሎም በምርጫው ድምጽ የሰጡ መራጮች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ እንደነበር ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።
የ49 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ሀገራቸውን ለሦስተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ነው በድጋሚ የተመረጡት።
በቀጣይ የሥራ ዘመናቸውም የሥራ ዕድል ፈጠራና ፖለቲካዊ መረጋጋትን ማስፈን ትልቁ የቤት ሥራቸው ይሆናል መባሉን ዘገባው አስታውሷል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!