የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለመበልፀግ በምታደርገው ጉዞ የማዕድን ዘርፉ ወሳኝ ሚና ይጫወታል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

By Amele Demsew

November 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለመበልፀግ በምታደርገው ጉዞ የማዕድን ዘርፉ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ዲፕሎማቶችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከሕዳር 14 እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው ሁለተኛው ዓመታዊ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ዛሬ ተከፍቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ኤክስፖውን ባስጀመሩበት ጊዜ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ለመበልፀግ ያላትን ፍላጎት እውን ለማድረግ ትኩረት አድርጋ ከምትሰራባቸው ዘርፎች አንዱ የማዕድኑ ዘርፍ ነው፡፡

ባለፋት አመታት ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት ለማወቅ ሲሰራ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በርካታ አስደማሚ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ሀብት እንዳላት ማረጋገጥ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በኤክስፖው ከ90 በላይ ኩባንያዎች እየተሳተፋ ሲሆን የወርቅ፣ የከበሩ ማዕድናት፣ የድንጋይ ከሰል፣ ብረት፣ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ማዕድን አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን እንደሚያስተዋውቁ ተገልጿል፡፡

የማዕድን ዘርፉ ልምድና ተሞክሮዎች፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የዘርፉ እድሎች ላይ ትኩረት ያደረገ ለሶስት ቀን የሚቆይ የፓናል ውይይትም ከኤክስፖው ጎን ለጎን እንደሚካሄድ ም ተገልጿል።

በቅድስት አባተ