አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃውቲ አማፂያን በእስራኤል የንግድ መርከብ ላይ የፈፀሙት ጥቃት ሳዑዲ አረቢያ በየመን የምታደርገውን የሰላም ጥረት ማስተጓጎሉ ተገለፀ፡፡
ባለፈው እሁድ በኢራን ይደገፋሉ የተባሉት የሃውቲ አማፂያን በቀይ ባህር ከቱርክ ወደ ህንድ በመጓዝ ላይ በነበረው የእስራኤል መርከብ ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈፀማቸው ይታወሳል።
ጥቃቱን ተከትሎ ለረጅም ጊዜ በሃውቲ አማፂያን እና በእስራኤል በኩል የሰላም ስምምነት እንዲደረግ በሳዑዲ አረቢያ ሲደረግ የነበረው ጥረት መስተጓጎሉ ነው የተገለፀው፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሳዑዲ አረቢያ የየመን ዲፕሎማቶችን በሪያድ በመጥራት የውጭ ሀይሎች በስድስት ወራት ውስጥ ከየመን እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች ተብሏል፡፡
እንግሊዝ እና አሜሪካ በሳዑዲ አረቢያ ሲሞከር የቆየውን ጥረት “የሃውቲ የሽብር ቡድኖችን ማጎልበት ነው” በሚል ስምምነቱን ሲቃወሙ እንደቆዩ ተጠቅሷል።
በተለይም አሜሪካ ከስምምነት ይልቅ በየመን ሰንዓ በሚገኙ የሃውቲ አማፂያን ወታደራዊ ጣቢያዎች እና በኦፕሬሽን ክፍሎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ማቀዷ ተገልጿል፡፡
አማፂያኑ ቀደም ሲል ኮርዳድ-3 የተባሉትን የኢራን የአየር መቃወሚያዎችን በመጠቀም የአሜሪካን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትተው ጥለዋል መባሉን ዘጋርዲያን አስነብቧል፡፡