አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የጸጥታ ምክር ቤት ምስረታና በክልሉ ሰላምና ጸጥታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የጸጥታ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ እንዳሻው ጣሰው እንደገለጹት፥ በክልሉ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በክልሉ ሰላምና አንድነትን የሚሸረሽሩ ጉዳዮችን በመለየት ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በቁጥጥር ስር በማዋል በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን ስንቆጣጠር ቆይተናል ብለዋል።
ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሃይል በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ በአካባቢ ተደራጅቶ ልዩ ልዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር የህዝብን የዕለት ተዕለት ስራ ለማወክ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ መቻሉንም አብራርተዋል።
በዛሬው እለት በይፋ ስራውን የሚጀምረው የጸጥታ ምክር ቤት ጉዳዮችን በአንክሮ በመከታተል ተወያይቶ ትላልቅ ውሳኔዎችን እንደሚያስቀምጥ ጠቁመዋል።
የክልሉን ጸጥታ ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ለጸጥታ አካላት፣ በየደረጃው ላሉ አመራሮች፣ ለህዝብ አደረጃጀቶች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች እና ለሃይማኖት አባቶች ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው፥ በክልሉ ቀደም ሲል ሳይፈቱ የቆዩ የጸጥታ ችግሮችን በመፍታት የክልሉን ህዝብ የመልማት ፍላጎት እውን ለማድረግ የጸጥታ ምክር ቤቱ የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በመከላከል ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ በመከተል ጠንካራ ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነ ማንሳታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክል፡፡
ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ስርዓት መከተል፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር፣ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር፣ የአብሮነት እና የመከባበር እሴቶችን ማጎልበት ላይ ትኩረት ይደረጋልም ነው ያሉት።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!