Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ለመገንባት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ለመገንባት ስምምነት ተፈራረሙ።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየሰጠ ካለው የጋዜጠኝነትና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ትምህርት በተጨማሪ በማህበረሰብ ሬዲዮ ተደራሽ ለመሆን አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ለዚህም ያግዝ ዘንድ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ስቱዲዮ ግንባታ ለማከናወን ከዩኒቨርሲቲው ጋር መስማማቱ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ÷ተቋማቱ ባላቸው የዳበረ እውቀትና ልምድ የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች ላይ ለመስራት ተስማምተዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው በወቅቱ እንዳሉት÷ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር ያለውን የቆየ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነው።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከዚህ ቀደም ለስልጤ ማህበረሰብና ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ደረጃቸውን የጠበቁ የማህበረሰብ ሬዲዮ ስቱዲዮ ግንባታ ማከናዎኑ ይታወሳል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቀደም ሲልም በጋራ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል።

አሁን ላይ መጠን ሰፊ ፕሮጀክት ይዘን በጋራ ለመስራት በመስማማታችን ደስተኞች ነን ሲሉም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚያበረክታቸውን የማህበረሰብ አገልግሎቶች ለማስፋት አጋዥ የሚሆነውን ስቱዲዮ ለመገንባት የተደረገው ስምምነትም ትብብሩን እንደሚያጠናክረውም ተናግረዋል።

ከፋና ጋር ስንሰራ በሙሉ እምነት የምንጠብቃቸውን ውጤቶች እንደምናገኝ አረጋግጠን ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ በተለይም የሚገነባው ስቱዲዮ ደረጃውን የጠበቀ እንደሚሆንና በፍጥነት እንደሚጠናቀቅ ተስፋ በማድረግ ነው ብለዋል።

በሙሉጌታ ደሴ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version