የሀገር ውስጥ ዜና

አሥተዳደሩ ከሸገር ከተማ ጋር በጋራ ለመሥራት ተፈራረመ

By ዮሐንስ ደርበው

November 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር እና የሸገር ከተማ አሥተዳደር የተቀናጀ ዲጂታል የመሬት ምዝገባን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረሙ፡፡

ሥምምነቱን የፈረሙት የአሥተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ እና የሸገር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ሥምምነቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ ዘመናዊ ከተማን እውን ለማድረግ የሚያስችል አሰራር አበልጽጎ ማስረከብ ሲሆን በ20 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት መሆኑን የአሥተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሥምምነቱ ከመሬት ምዝገባ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሠነዶችን ዲጂታይዝ ማድረግ፣ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት፣ የዲጂታል ክፍያ የካዳስተር ሥራ፣ የመሬት ምዝገባን ከሌሎች አገልግሎቶች ጋር የማስተሳሰር፣ በከተማው ያለውን የመሬት ሀብት፣ የባለቤትነት ማረጋገጫ፣ የመረጃውን ደኅንነት የመጠበቅና ስልጠና የመስጠት ሥራዎችን ያካተተ መሆኑን አቶ ሰለሞን ሶካ ተናግረዋል፡፡

አሥተዳደሩ ደኅንነቱ የተጠበቀ ‘ስማርት ሲቲን’ እውን ለማድረግ የሚያስችል አሰራር አበልጽጎ በተያዘው ጊዜ እንደሚያስረክብም አረጋግጠዋል፡፡

አሰራሩ ለአሥተዳደር ምቹ፣ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል፣ መንገድ፣ መብራት፣ ውኃ፣ የፖሊስ ሥራን የመሳሰሉትን ሁሉ የሚያሳልጥ፣ ለዜጎች ምቹና ማራኪ የሆነ ኢንቨስትመንትን የሚጋብዝና ምርታማነትን የሚጨምር ነው ብለዋል፡፡

ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ሸገር ከተማን ‘ስማርት ሲቲ’ ለማድረግ የተያዘውን ዓላማ ለማሳካት የመሬት ምዝገባ (የካዳስተር) ሥራዎች ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በከተማዋ የሚታየውን ያልተደራጀ እና የተበጣጠሰ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓት ወጥ ወደ ሆነ እና በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ በመሥራት ሸገርን ‘ስማርት ሲቲ’ ለማድረግ ከአሥተዳደሩ ጋር በቅርበት እንሠራለንም ነው ያሉት።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!