ብዙ ማይሎችን በማቋረጥ የአደንዛዥ እጽ ዝውውርን ድል ያደረገችው ህንዳዊ ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንዳዊቷ የፖሊስ አባል ፕሪትፓል ኮር በተለያዩ ግዛቶች ብዙ ማይል ርቀቶችን በመጓዝ ታጣቂዎችን እና የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎችን እንቀስቃሴ ድል ማድረግ መቻሏ ተነግሯል፡፡
ህንድን በሰሜን ምስራቅ በምታዋስናት ማይናማር ድንበር በኩል የታጣቂ ተገንጣይ ቡድኖች እንቅስቃሴ፣የአደንዛዥ እጽ ዝውውር እና ሱስ ለህንድ እና ለአካባቢው ሀገራት ለዓመታት ከባድ የማህበራዊ ቀውስ ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡
ኔጋላንድ እና ማኒፑር ከተባሉ አካባቢዎች በሚነሳው የአደንዛዥ እጽ ዝውውር ምክንያትም ሰሜን ምስራቅ ህንድ ታይላንድ እና ላኦስ ድምበሮች አካባቢ የሚገኙ ዜጎቸ ለአደዣዥ እጽ ዝውውር እና ሱስ ተጋላጭ ሆነዋል፡፡
በህንድ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣናት እና የማዕከላዊ የስለላ ኤጀንሲዎች የሚሰሩበት የኢንዲያን ፖሊስ ሰርቪስ አባል የሆነችው ፕሪትፓል ኮር የተፈጠረውን ችግር ከስሩ ለማድረቅ የሄደችበት ርቀት አድናቆትን አትርፎላታል፡፡
ኮር አደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎችን በቀጥታ ከመዋጋት ይልቅ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረቷን በማድረግ ችግሩ በዋናነት በተስፋፋበት የኔጋላንድ ግዛት ወጣቶችን በማሰባሰብ የጉዳዩን አሳሳቢነት ማስገንዘብ ትጀምራለች፡፡
ጥቂት ወጣቶችን በማሰባሰብ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዋን የጀመረችው ኮር ስራዋን በማስፋፋት በህንድ ናጋላንድ፣ኖክላክ እና ሎንግሌግ በተባሉ ስፍራዎች የግሏን የኮሚኒቲ ፖሊስ በመመስረት ለ3 ዓመታት ስራዋን አጠናክራ ቀጠለች፡፡
ብርቱዋ ፖሊስ በአካባቢው በአደንዛዥ እጽ የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚስያችል የተሃድሶ ማዕከል በመክፈትም ተጠቂዎች ከሱሳቸው በመላቀቅ በእርሻና በሽመና ስራዎች እንዲሰለጥኑ ማድረጓም ተመላክቷል፡፡
በዚህም በርካታ ወጣቶችን ከሞት ማትረፍ የቻለችው ኮር በዚህ ድርጊት የሚሰማሩ ወጣቶች በአብዛኛው የሚመጡት ምንም አይነት መተዳደሪያ ከሌላቸው ድሃ ቤተሰቦች እንደሆነ ትናገራለች።
ወጣቶች ድጋፍ ከተደረገላቸው መቀየር ይችላሉ የምትለው ፖሊሷ÷ ባደረገችው ጥረት ከ480 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ከሱስ ሕይወት በማውጣት በተለያዩ ስራዎች እንዲሰማሩ ማድረግ መቻሏን ገልጻለች፡፡
በዚህ ጥረቷም ወጣቷ ፖሊስ በህንድ ሰሜን ምስራቅ ክፍል አሳሳቢ የነበረውን የአደንዛዥ እጽ ዝውውር እና የማፍያ ቡድኖችን እንቀስቃሴ በእጅጉ መቀነስ የቻለች ሲሆን÷ ከህንድ መንግስትም ከፍተኛ አድናቆት እና ምስጋና ተችሯታል፡፡
አሁን ላይም ከአደንዛዥ እጽ በተጨማሪ በአካባቢው የሴቶችን የወር አበባ እና የንጽህና አጠባበቅ በተመለከተ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዋን አጠናክራ እንደቀጠለች አር ቲ ፊቸር አስነብቧል፡፡