ዓለምአቀፋዊ ዜና

ወደ ጋዛ የተቋረጠው ሰብዓዊ አቅርቦት “በፍጥነት እና በዘላቂነት” እንዲቀጥል “ብሪክስ” ጠየቀ

By Alemayehu Geremew

November 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ጋዛ የተቋረጠው ሰብዓዊ አቅርቦት “በፍጥነት እና በዘላቂነት” እንዲቀጥል ብሎም ሁለቱም ወገኖች ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ የ”ብሪክስ” ቡድን አባል ሀገራት ጥሪ አቀረቡ፡፡

ሀገራቱ ጥሪያቸውን ያቀረቡት በትናንትናው ዕለት በእስራዔል-ሃማስ ጦርነት ላይ ለመምከር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ያካተተ ውይይት በበይነ መረብ ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡

“ብሪክስ” በተለይ አሁን ላይ በጋዛ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ እጅግ እያሳሰበው መሆኑንም ትናንት የቡድኑ አባል ሀገራት ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ ተመላክቷል፡፡

መግለጫው በተለይ የእስራዔል-ሃማስ ጦርነት እየተባባሰ መሄድ የቡድኑን አባል ሀገራት ይበልጥ እያሳሰበ መምጣቱንም አንስቷል፡፡

አባል ሀገራቱ ምንም ባላጠፉ ንፁሐን የፍልስጤም እና እስራዔል ሕዝቦች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የጦር ወንጀል እንደሆኑ ጠቁመው ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡

በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ሕግ እና መብት መሠረት ንፁሐን ሙሉ ጥበቃ እና አሥፈላጊው ክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ጦርነቱን ተከትሎ የታገቱ ንፁሐን ደኅንነት እና ሰብዓዊነት ተጠብቆ በፍጥነት እና ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲለቀቁም ጠይቀዋል፡፡

በዓለም አቀፉ ሕግ እና ደረጃ መሠረት በእስራዔል እና ሃማስ ጦርነት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍንም ሀገራቱ መጠየቃቸውን አኒ አስነብቧል፡፡

ፍልስጤማውያንን ከጋዛም ሆነ ከአዋሳኝ ሀገራት በማስገደድ ማፈናቀል፥ የጄኔቫን ሥምምነት እና ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ሕግ የሚጥስ የጦር ወንጀል መሆኑም ተነስቷል፡፡

መግለጫው የዓለምአቀፉ የሰብዓዊ ሕግ እንዲከበር እና የሰብዓዊ አቅርቦቶች በጦር ቀጣናው ላሉ ንፁሐን ያለአድልዖ እንዲደርስም ጠይቋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች ችግራቸውን በመነጋገር እና አካታች የውይይት መድረክ በመፍጠር ሠላም ለማስፈን እንዲሠሩም አባል ሀገራቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡