አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነት ውስጥ የሚገኙት እስራኤል እና ሃማስ ለአራት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነቱ በኳታር አሸማጋይነት በዶሃ በተካሄደ ምስጢራዊ ድርድር የተደረሰ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ተፋላሚቹ የተኩስ አቁም የሚጀምሩበት ቀንም በቀጣዮቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡
በስምምነቱ መሰረትም ሃማስ እስካሁን አግቶ የያዛቸውን 50 እስራኤላውያን ለመልቀቅ መስማማቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በምትኩም በእስራኤል እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ 150 ፍልስጤማውያን እንደሚፈቱ ስምምነትላይ መደረሱ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ባለፈም የተኩስ አቁሙ በመቶዎች የሚቀጠሩ የሰብዓዊ እርዳታ፣ ነዳጅ እና መድሃኒቶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ያስችላል ተብሏል፡፡
ለዚህም ለአራት ቀናት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ሁሉም አካባቢዎች ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማትችል ተገልጿል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንሚያን ኔታንያሁ÷ በስምምነቱ በጋዛ ሀማስ እስካሁን ያገታቸው 50 እናቶች እና ሕጻናት በአራት ቀናት ውጥት እንደሚለቀቁ ተናግረዋል፡፡
እስራኤል በሃማስ የታገቱ ዜጎቿን ለማስለቀቅ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ገልጸው÷ ለዚህም የእስራኤል ካቢኔ የታገቱትን ነጻ ለማውጣት የተደረሰውን ስምምነት ማጽደቁን ጠቁመዋል፡፡
በእስራኤል እና ሃማስ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በአሜሪካ ፣ ሩሲያ እና በአውሮፓ ህብረት አድናቆት እንደተቸረው በዘገባው ተመላክቷል፡፡