የሀገር ውስጥ ዜና

የባንክ ካዝና በመስበር ገንዘብና አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከጥይት ጋር ዘርፈዋል የተባሉ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ

By Meseret Awoke

November 21, 2023

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 11 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወጋገን ባንክ የረር ቅርንጫፍን ካዝናን በመስበር ገንዘብና አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 ጥይት ጋር ዘርፈዋል ተብለው የተከሰሱ ስምንት ተከሳሾች እስከ 8 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች 1ኛ ገበያው ምስጋናው፣ 2ኛ እዮብ ተመስገን፣ 3ኛ የሆቴል ባለቤት ነው የተባለው ይርጋለም አድማሱ፣ 4ኛ ተሾመ ደምሴ ፣ 5ኛ ሀይለማርያም መለሰ፣ 6ኛ ጥላሁን ወልዴ፣ 7ኛ ጌታሁን ተፈራ እና 8ኛ ተከሳሽ አቤል ንጉሴ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የቦሌ ምድብ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ሁለት የወንጀል ክስ ያቀረበባቸው ሲሆን በአንደኛው ክስ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ አምስት ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ነው።

ይህም ክስ ” ገበያው ምስጋናው የተባለው አንደኛ ተከሳሽ በወጋገን ባንክ የረር ቅርጫፍ በጥበቃ ሰራተኛነት ሲሰራ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 3:00 ሰዓት ላይ የዕለቱ ተረኛ ጥበቃ ሰራተኛን በማገትና እጅና እግሩን በገመድ በማሰርና አፉን በፕላስተር በማፈን የባንኩን የገንዘብ ካዝና በፌሮ ብረት በመስበር 409 ሺህ 172 ብር በጥሬ እንዲሁም አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 ጥይት ጋር ዘርፈዋል” ሲል ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

ሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ6ኛ እስከ 8ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን፥ ከላይ የተጠቀሱ አምስት ተከሳሾች ከወጋገን ባንክ ጃክሮስ ቅርንጫፍ ዘርፈዋል የተባለውን አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 ጥይት ጋር 6ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ወልዴ ገዝቶ ለ7ኛ ተከሳሽ ለጌታሁን ተፈሩ መሸጡ በክሱ ተጠቅሷል።

7ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ8ኛ ተከሳሽ አቤል ንጉሴ ደላላነት መሳሪያውን ለሌላ ላልተያዘ ግለሰብ በመሸጥ በአጠቃላይ በከባድ የውንብድና ወንጀል የተከሰሱ ናቸው።

በክሱ ላይ ወንጀሉ ተፈጽሟል በተባለበት ቀን የዕለቱ ተረኛ ጥበቃ አባል እጅና እግሩን በገመድ በማሰር በህይወት ይኑር አይኑር ባልተለየበት ሁኔታ የደረሰበት እንደማይታወቅ ዐቃቤ ህግ ጠቅሶ ነበር።

ተከሳሾች ክሱ ከደረሳቸውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ”ወንጀሉን አልፈጸምንም’ ሲሉ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ስድስት ምስክሮችን በተለያዩ ቀናቶች አቅርቦ አሰምቷል።

ችሎቱ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን መርምሮ ተከሳሾቹ ገንዘብ እና የአንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 ጥይት ጋር በተደረገ የዝርፊያ ወንጀልን በሚመለከት ብቻ የምስክርነት ቃል መሰረት እንዲከላከሉ በአብላጫ ድምጽ ብይን ተሰጥቶ ነበር።

ወንጀሉ ተፈጽሟል በተባለበት ወቅት አንድ ተረኛ ጥበቃ አባል እጅና እግሩን በገመድ ታስሮ ተከሳሾቹ የት እንዳደረሱት እንደማይታወቅም ዐቃቤ ህግ ጠቅሶ ያቀረበውን ክስ በሚመለከት ግን በቀረቡ ምስክሮች ግለሰቡ ጉዳት ደርሶበት ስለመሰወሩ የሚገልጽ ማስረጃ ባለመቅረቡ ውድቅ አድርጎታል ።

እንደ አጠቃላይ ፍርድ ቤቱ ከባድ የተደራጀ የውንብድና ወንጀል የሚለውን የክስ አንቀጽ በመቀየር በውንብድና ብቻ በሚል አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

በዚህ ወቅት ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያሉ ተከሳሾች ከማረሚያ ቤት የቀረቡ ሲሆን 6ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ግን በተፈቀደላቸው የ13 ሺህ ብር ዋስ በውጭ ሆነው በችሎት ቀርበዋል።

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ከሚያዚያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ቀናቶች የተመለከተ ሲሆን ባቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ ግን የዐቃቤ ህግን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው እንዲከላከሉ በተባሉበት አንቀጽ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ በዚህ መልኩ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ 1ኛ ተከሳሽን በስምንት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

2ኛ እና 7ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ደግሞ እያንዳንዳቸው በሰባት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

ቀሪ ተከሳሾችን ማለትም የተሰረቀ መሳሪያን ሸሽገዋል ተብለው የተከሰሱትን እና ጥፋተኛ የተባሉት ከ6ኛ እስከ 8ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን በሚመለከት እስከ አንድ አመት ከስድስት ወራት በሚደርስ ቀላል እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

በሌላ በኩል በተመሳሳይ በውንብድና ወንጀል በሌላ መዝገብ ተከሰው ጉዳያቸው ለብቻ ሲታይ የነበሩት የሆቴል ባለቤት ነው የተባለው ይርጋለም አድማሱ እና አለሙ አሰፋ የተባሉ ተከሳሾች በተከሰሱበት ከባድ የውንብድና ወንጀል ይርጋለም አድማሱ በሰባት አመት ከ3 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነ ሲሆን አለሙ አሰፋ ደግሞ በሰባት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

በሁለቱም መዝገብ ይርጋለም አድማሱ የተባለው ተከሳሽ በድምሩ 14 አመት ከ3 ወራት ጽኑ እስራት ቅጣት ተጥሎበታል።

የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተከሳሾቹ የተጣለባቸውን የጽኑ እስራት ቅጣት እንዲያስፈጽም ታዟል።

በታሪክ አዱኛ