Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር በእጅጉ መሻሻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታው በእጅጉ መሻሻሉን የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው ÷ክልሉ ከነበረበት የጸጥታ ችግር አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ መሻሻል እና የሰላም ሁኔታው ቢቀየርም አሁንም ቢሆን ማኅበረሰቡ የሚፈልገው የሰላም ዓየር ሙሉ ለሙሉ መጥቷል ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

የሐሳብ አማራጮችን በውይይት እና በንግግር ማቅረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ሃላፊው፡፡

የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ፣ ከቀን ወደ ቀን እየተስተካከለ የመጣ እና የተሻለ የሰላም ዓየር ቢኖርም አሁንም ሥራ የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸውንም ነው ያመላከቱት፡፡

ለመጣው የሰላም መሻሻል የሕዝቡ ተሳትፎ እንዲሁም ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ያለው ቅንጅት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የሕዝብ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ደሳለኝ÷ ከሕዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች በችግሮች ላይ ለመነጋገር ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል፡፡

መንግሥት መፍታት የሚገባው ዋና ዋና ጉዳዮችና ችግሮችን በውይይት እንጂ ውስጥን በማዳከም መፍታት እንደማይቻልም ሕዝቡ ማንሳቱን ነው የጠቆሙት፡፡

ሕዝቡ እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ትክክል አለመሆኑን እየገለጸ ነውም ብለዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው ችግር የሕዝብን የልማት እንቅስቃሴ መገደቡን እና የኑሮ ውድነቱን ማባባሱን ገልጸው÷ ሰላምና ደኅንነትን የማስከበር ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም የሕዝቡ አስተዋጽዖም ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ሕዝቡ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው÷ በትክክልም ከአማራ ሕዝብ የሚጠበቅ እና ለነገ የሚሆኑ ሐሳቦች በውይይቶች እየተነሱ ነው፤ ለመሪዎችም ስንቅ የሆነ ሐሳብ እየተገኘ ነው ብለዋል፡፡

ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቻችን እናስፈታለን፣ ሰላማችንንም እንጠብቃለን እያለ ነው ብለዋል አቶ ደሳለኝ፡፡

መንግሥትም ጥያቄዎችን በጊዜ መፍታት እንደሚገባው፣ በቶሎ የማይፈቱትን ጥያቄዎች መቼ እና እንዴት ሊፈቱ እንደሚችሉ ማመላከት አለበት የሚሉ ሐሳቦች ከሕዝቡ እየተነሱ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ለክልሉ ሰላም መሆን የሕዝቡ ትብብር እያደገ መምጣቱንም ነው አቶ ደሳለኝ ያስረዱት፡፡

Exit mobile version