የሀገር ውስጥ ዜና

በ25 የገጠር ከተሞች የተጀመረው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

November 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ25 የገጠር ከተሞች የተጀመረው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትአስታወቀ።

አገልግሎቱ የገጠር ከተሞችን በፀሐይ ኃይል ማመንጫ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ በሰባት ክልሎች ሥር በሚገኙ 25 የገጠር ከተሞች “የሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት” ቀርፆ ወደ ሥራ መግባቱን አመላክቷል።

የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ፥ ግንባታው በአራት ተቋራጮች በስድስት ሎት ተከፍሎ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 145 ሺህ 169 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፥ አጠቃላይ ስምንት ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ይህ ፕሮጀክት 68 ነጥብ 7 የመካከለኛና 233 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መሥመር ዝርጋታ ይከናወንበታል ብለዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ