የሀገር ውስጥ ዜና

ነዋሪው ለውይይት ቅድሚያ በመስጠቱ ምሥጋና ይገባዋል – የጎንደር ከተማ አሥተዳደር

By Shambel Mihret

November 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተረጋጋና በሰከነ መንገድ ለውይይት በመቅረብ ነዋሪው ያደረገው መልካም ትብብር የሚመሰገን መሆኑን የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ገለጹ፡፡

በጎንደር ከተማ የተካሄዱ የውይይት መድረኮች በሰላም መጠናቀቃቸውን ተከትሎ አቶ ባዩህ አቡሃይ በሰጡት መግለጫ÷ ውይይቶቹ ለከተማዋ የወደፊት ለውጥ መሰረት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡

የመድረኮቹ ዓላማ÷ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅና የፀጥታ ሁኔታውን ዘላቂ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መግባባትን መፍጠር መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚቻልባቸውን መንገዶች ማመላከትም የውይይቶቹ ዓላማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በነዋሪዎቹ በኩል ለተነሱት የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነትና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች አሥተዳደሩ በቂ ምላሽ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

በከተማዋ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ትኩረት ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡

በመድረኮቹ ከተነሱት መካከል አብዛኞቹ ጥያቄዎች በነዋሪው ድጋፍ እንደሚመለሱ አስገንዝበው÷ ከሁሉም በላይ ሰላም ይቀድማልና ለከተማዋ ሰላም ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ከ19 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የተሳተፉባቸው መድረኮች አስተማሪና የቀጣይ ትኩረታችንን የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።

በሙሉጌታ ደሴ