የሀገር ውስጥ ዜና

ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ በትብብር እንደምትሰራ ገለጸች

By Melaku Gedif

November 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ኅዳር 7 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ፕሬዚዳንት ቻንግ ዋንሳምን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ በኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ስላለው ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል፡፡

አቶ ደመቀ÷ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር ያላት ጠንካራ ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ደቡብ ኮሪያ በዘላቂ ልማት ዙሪያ ጠንካራ ተሞክሮ ያላት መሆኑንና ኢትዮጵያም ይህንኑ የኮሪያ ልምድ እንደ ተሞክሮ እንደምትወስድ ገልጸዋል።

ቻንግ ዋንሳምን በበኩላቸው÷ ደቡብ ኮሪያ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው የልማት ሸሪኮች አንዷ መሆኗን አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ በ18 ፕሮጀክቶችና ሶስት የስልጠና ፕሮግራሞች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይ በተለያዩ የልማት መስኮች እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰራ መግለጻቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡