Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ስራ አጥነትን ለመቀነስ ወጣቶችን ከኢንዱስትሪ ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስራና ሰራተኛን በማገናኘት የስራ አጥነት ችግርን ለመቀነስ ወጣቶችን ከኢንዱስትሪ ጋር ማስተሳሰር ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ላይ ስልጠና ያጠናቀቁ 5 ሺህ 193 ወጣቶች ተመርቀዋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ እንደገለጹት÷ ከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ ባለው የስራ ዕድል ፈጠራ ስራ በርካቶችን ከስራ በማገናኘት ራሳቸውን እንዲችሉና ሀብት እንዲፈጥሩ አድርጓል::

ከተማ አስተዳደሩ የሰለጠነ የሰው ኃይል ዕጥረት እያለ ብዙዎች ስራ ፈላጊ የሆኑበት ሁኔታ ለማስተካከልም ወጣቶችን ከኢንዱስትሪ ጋር በማገናኘት በአስተሳሰብ ተቀይረውና በክህሎት በቅተው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ዛሬ የተመረቁት ሰልጣኞችም የዚሁ ስራ አንዱ አካል መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሁለተኛው ዙር የስልጠና መርሐ -ግብር ከ15 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን መግለጻቸውን የከተማው ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የከተማው ወጣቶችም ከተማ አስተዳደሩ በሚፈጥራቸው ዕድሎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል::

Exit mobile version