ዓለምአቀፋዊ ዜና

የማላዊ ፕሬዚዳንት በራሳቸውና ካቢኔያቸው ላይ የውጪ ሀገራት ጉዞ እገዳ ጣሉ

By Melaku Gedif

November 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማላዊ ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ (ዶ/ር) በራሳቸው እና ካቢኔያቸው ላይ የውጭ ሀገራት ጉዞ እገዳ መጣላቸው ተሰምቷል፡፡

የጉዞ እገዳው የሀገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም 44 በመቶ መዳከሙን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ለዚህም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ለማላዊ ኢኮኖሚ ማገገሚያ የሚውል 175 ሚሊየን ዶላር ብድር አጽድቋል፡፡

ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ በየትኛውም እርከን የሚገኝ አመራር እስከ መጪው መጋቢት ወር ድረስ በመንግስት ገንዘብ ምንም አይነት የውጭ ሀገር ጉዞ ማድረግ አይችልም ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በውጪ ሀገራት የሚገኙ ሚኒስትሮችም በፍጥነት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ነው ትዕዛዝ ያስተላለፉት፡፡

ለከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ይሰጥ የነበረው የነዳጅ ጥቅማጥቅም በ50 በመቶ እንዲቀንስ መወሰናቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የማላዊ ገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከሙን ተከትሎ አሁን ላይ በሀገሪቱ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከመኖሩ ባለፈ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት መከሰቱ ተጠቁሟል፡፡