የሀገር ውስጥ ዜና

የባህር በር ጥያቄው ለምስራቅ አፍሪካ የመልማት ዕድል ይዞ የሚመጣ ትልቅ አጋጣሚ ነው – ምሁራን 

By Amele Demsew

November 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እያነሳች ያለችው የባህር በር ጥያቄ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንድነትን የሚፈጥርና ትልቅ የመልማት እድል ይዞ የሚመጣ ዕድል እንደሆነ ምሁራን ገለጹ፡፡

የባህር በር ጥያቄን በተመለከተ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራን እንደገለጹት÷ የባህር በር ጥያቄውን የቀጣናው ሀገራት እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደው ለጋራ ልማት ሊጠቀሙበት ይገባል።

በተለያዩ አደረጃጀቶች ጥምረት በመፍጠርም አንድነታቸውን ለማጠንከር ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የህግ ባለሙያው ወንድሙ ኢብሳ እንደሚሉት÷ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በትብብርና በጋራ በተለያዩ አደረጃጀቶች ጥምረት ፈጥረው በጋራ መልማት የሚችሉበት መንገድ መፍጠር አለባቸው።

የባህር በር ጥያቄም ሊቆም የማይችልና ከትውልድ ትውልድ ሊሸጋገር የሚችል እንደሆነ አመልክተዋል።

በመሆኑም ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ የማንንም ሀገር ሉዓላዊነት ሳይነካ ምላሽ የሚያገኝ ተገቢ ጥያቄ መሆኑን ጠቁመዋል።

የታሪክ ምሁሩ አየለ በከሪ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የፓን አፍሪካን መርህ ተከትለውና አንድ ህዝቦች መሆናቸውን ተረድተው ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በቀጣናው ሀገራት ሰጥቶ በመቀበል መርህ ስምምነት ላይ ከተደረሰም ለጋራ ተጠቃሚነት እንደሚረዳ አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ሀገርም ጥበብ የተሞላበትና ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥያቄም ከወደብ ባሻገር ቀጣናውን ጠንካራ አድርጎ የማውጣት ትልም የያዘ መሆኑ አግባብነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡