የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ደመቀ መኮንን በአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ተወያዩ

By Alemayehu Geremew

November 15, 2023

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 5 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሪታ ላራንጂንሃ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይ መክረዋል።

በዚህ ወቅት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን አጋርነት እና ትብብር መደበኛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

በሁለቱ ወገን በኩል በየዘርፉ የሚደረግ ውይይት አስፈገላጊነትን ያነሱት አቶ ደመቀ፥ ኢትዮጵያ የፊታችን ታህሳስ ወር ለሚደረገው ስብሰባ ያደረገችውን ዝግጅት በተመለከተ አስረድተዋል።

አቶ ደመቀ አያይዘውም መንግስት በትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

በተጨማሪም ከብሄራዊ ምክክር እና ከሽግግር ፍትህ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሪታ ላራንጂንሃ በበኩላቸው÷ በአውሮፓ ኅብረት እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን አድንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቷን ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረትም የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የአውሮፓ ኅብረት እስከ መጨረሻው አሥፈላጊውን ሁሉ ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አምባሳደር ሪታ አረጋግጠዋል፡፡