የሀገር ውስጥ ዜና

የፕሪቶሪያው ስምምነት እናቶች ተጨማሪ ልጆች እንዳይሞትባቸው አድርጓል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

By Amele Demsew

November 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪቶሪያው ስምምነት ቢያንስ ቢያንስ ለኢትዮጵያ እናቶች ተጨማሪ ልጆች እንዳይሞትባቸው ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም÷ ከስምምነቱ በኋላ ተጨማሪ ሰዎች እንዳይሞቱ ማድረግ መቻሉን በአጽንኦት ገልጸው ከዚህ አንጻር በፕሪቶሪያ የተደረገውን ስምምነት በቀላሉ ማየት እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡

ከስምምነቱ በኋላ በትግራይ ክልል ተቋርጠው የነበሩ የኤሌክትሪክ፣ የስልክ፣ የትራንስፖርት፣ ባንክና መሰል አገልግሎቶች በስፋት እንዲጀመሩ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም÷ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መደረጉንና ለክልሉ በጀት መፈቀዱን ገልጸዋል፡፡

ቀሪ ሥራዎችንም የፌዴራል መንግስት ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች ጋር በመተባበር በቀጣይ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው