Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች፡-

እያንዳንዱ ችግር ብለን የምናነሳው ሀሳብ አሁን የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን ተሳስሮ የመጣ ስለሆነ እነዚህን ጉዳዮች ከስር መሰረቱ መገንዘብና ማየት ካልቻልን መፍትሔ ለማምጣት እንቸገራለን፡፡
ልንግባባበት የሚገባው ዋና ጉዳይ ችግሮቻችን በጋራና እኩል የምንገነዘባቸውና የምንረዳቸው ከሆኑ ጉዟችን ወደ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡
በችግሮች ላይ የማንግባባ ከሆነ ግን የመፍትሄ አማራጩ ምንም ይሁን ምን ውጤታማ ለመሆን ያስቸግራል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለው አብዛኛው የችግር ትንታኔ ስሜት ይጫነዋል፡፡
ስሜት የሚጫነው የችግር ትንታኔ ደግሞ አያግባባም፤ እንዲሁም የሴራ ትንታኔም ይበዛዋል፡፡
ሁኔታውን እንዳለ ማየት ሳይሆን የሚተነተኑ ጉዳዮች አሉ፣ ህዳሴን እንሰራለን ሲባል፤ የባህር በር እንፈልጋለን ሲባል፤ ተቸግረው ነው ያስፈልጋቸዋል ሳይሆን ሌላ ሀገር ላይ ጉዳት ሊያመጡ ነው የሚባሉ መሰረት የሌላቸው ትንታኔዎች ችግሩን በትክክል እንዳንገነዘብ ያደርጉናል፡፡ ከእውነትም ያርቁናል የተስተካከለ መፍትሄ ለማምጣትም ያስቸግራሉ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ህገ ደንብ አሳታፊ፣ አካታችነትና ህብረ ብሄራዊነት የሚንጸባረቅበት ነው፤ በጋራ በመኖር በጋራ መበልጸግ እንችላለን የሚል እምነት ብልጽግና ውስጥ አለ፣ በተለያዩ ዘርፎች በትጋት በመስራት ሀገራችን ማበልጸግ አለብን፣
ሰላም በማስቀደም ንግግርን በማስቀደም ሀገራችን ወደ ብልጽግና እንድታመራ ማድረግ አለብን፤
ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች ያሉ ቢሆንም፤ ዋነኛው ችግር አባባሽ ጉዳይ ነጠላ ትርክት ነው፤ ከፋፋይና እና የሚለያይ ትርክት ሀገር አፍራሽ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፤ ታላቅ ትርክት ህዝብ ይሰበስባል፤ ነጠላ ትርክት ደግሞ ህዝብን ይከፋፍላል፣
የባህር በር እንፈልጋለን ሲባል ተቸግረው ነው ያስፈልጋቸዋል ሳይሆን ሌላ ሀገር ላይ ጉዳት ሊያመጡ ነው የሚባሉ መሰረት የሌላቸው ትንታኔዎች ችግሩን እንዳንገነዘብ ያደርጉናል፣ ከእውነት ያርቁናል፣
እንደ ብልጽግና ልዩ ልዩ ሃይማኖት፣ እሳቤና ሌሎች እሴቶችን አካቶ ህብረ ብሄራዊነትን የተቀበለች ኢትዮጵያን መገንባት እንፈልጋለን፡፡
ታሪክን በሚመለከት ሁሉም ሰው ታሪክን እኩል ሊረዳው ስለማይችል ትርጉሙን ለባለሙያዎች ብንተው መልካም ነው፡፡
መንግስትን ታጥቆ ማሸነፍ አይቻልም ከባድ ነው ይህ መንግስትን በትጥቅ እናስወግዳለን የሚሉ ሰዎች ሊያውቁት ይገባል፡፡
በየሻምበል ምሕረትና አመለወርቅ ደምሰው
Exit mobile version