የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ መላኩ አለበል በሐዋሳ ከተማ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኙ

By Shambel Mihret

November 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ህዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኙ፡፡

አቶ መላኩ አለበል በጉብኝታቸው ድግስ የአዮዲን ጨው ማምረቻን፣ያሬድ ኢንጂነሪንግን፣ “ሱፐር ኦቫ እና ታቦር ሴራሚክስ” ኢንዱስትሪዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት አቶ መላኩ አለበል÷ ኢትዮጵያ የያዘችውን የልማት ጎዳና ለማፋጠን አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ቁሳቁሶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለኢንዱስትሪዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በበኩላቸው፥ በክልሉ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ዘርፉ ለኢትዮጵያ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በክልል ደረጃ ተስፋ ተጥሎበታልም ነው ያሉት።

አምራች ኢንዱስትሪዎችም የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡