የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ወጣቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን እንዲተገብሩ እየታገዙ መሆኑ ተገለጸ

By Amele Demsew

November 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ወጣቶች የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅመው የህዝቡን ችግር የሚፈቱ ፕሮጀክቶችን እንዲተገብሩ እየታገዙ መሆኑ ተገልጿል ፡፡

በአፍሪካ የመጀመሪያው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) የተማሪዎች የውድድር ኤክስፖ በአዲስ አበባ በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት እየተካሄደ ነው።

ዝግጀቱን አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ከኤቱኤስቪ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባባር አዘጋጅተውታል፡፡

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ተማሪዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያበለጸጓቸውን ምርቶች ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡

የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ዋና ዳይሬክተር ውባየሁ ማሞ (ኢ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ በመርሐ-ግብሩ በአፍሪካ ወጣቶች የተሰሩ በርካታ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስራዎች ለእይታ መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ለእይታ ከቀረቡት ስራዎች መካከልም በህክምና፣ በትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በምህንድስና ዘርፍ የበለጸጉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ወጣቶች የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅመው የህዝቡን ችግር የሚፈቱ ፕሮጀክቶችን እውን እንዲያደርጉ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የኤቱኤስቪ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤምኔ ቫራ በበኩላቸው ÷ በአፍሪካ የመጀመሪያ በሆነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት የተማሪዎች ውድድር ኤክስፖ ከ47 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 3 ሺህ 700 ሥራ ፈጣሪዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከውድድሩ ተሳታፊዎች መካከል ስምንት ተወዳዳሪዎች ለመጨረሻው ዙር ውድድር ያለፉ መሆናቸውን ገልጸው ፥ተወዳዳሪዎቹም ከኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ቱኒዚያ፣ ናሚቢያ፣ እና አልጄሪያ የመጡ ናቸው መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የአውደ-ርዕዩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት እንደዚህ ዓይነት መድረኮች አፍሪካውያን ወጣቶች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ነውም ብለዋል፡፡