Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምንነትና ህክምናው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ማለት የማሕጸን ጫፍ የምንለው የሰውነት ክፍል ላይ የሚከሰት የካንሰር አይነት ነው፡፡

የማህጸን በር ካንሰር ምንነትና ህክምናውን በተመለከተ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ከሆኑት ዶ/ር ዳዊት መስፍን ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ዶ/ር ዳዊት የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር የሚመጣው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ (ኤች ፒ ቪ) 16፣17 እና በሌሎችም የቫይረሱ ዝርያዎች መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ለቫይረሱ አጋላጭ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል ደግሞ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክሙ የኢንፌክሽን በሽታዎች፣ ጾታዊ ግንኙነት ቶሎ መጀመርና ከብዙ ሰዎች ጋር ጾታዊ ግንኙነት ማድረግ ተጠቃሽ እንደሆነም ነው የሚገልጹት።

ቫይረሱ ወደ ካንሰርነት ከመቀየሩ በፊት ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ በአማካይ ከ10 እስከ 15 ዓመት ሊቆይ እንደሚችልም ጠቅሰዋል።

ወደ ካንሰር ከተቀየረ በኋላ እንደ ህመሙ ደረጃ ምልክቶቹ የተለያዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዶክተር ዳዊት ያስረዳሉ፡፡

ከምልክቶቹ መካከልም በጾታዊ ግንኙነት ወቅት እና ከጾታዊ ግንኙነት በኋላ መድማት መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ሊኖር እንደሚችል ያስረዳሉ።

በሽታው ከማህጸን አልፎ ወደ ማህጸን ግድግዳና አካባቢ መሰራጨት ሲጀምር ደግሞ የሽንት መቆጣጠር ችግር፣ የሽንት ከለር መቀየር፣ ለመሽናት መቸገርና ሌሎች መሰል ምልክቶች ሊታዩ እንደሚችሉም ነው የሚናገሩት።

በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከልም ጾታዊ ግንኙነት በለጋ እድሜ አለመጀመር (ከ19 ዓመት በፊት አለመጀመር)፣ ጾታዊ ግንኙነት ከተጀመረ በኋላም ጥንቃቄ የተሞላበት ግንኙነት ማድረግ እንዲሁም ክትባት መውሰድ እንደሚገባም አስረድተዋል።

ወደ ካንሰር ከተቀየረ በኋላ የመጀመሪያው ደረጃ ካንሰሩ ከማህጸኑ ጫፍ ላይ ብቻ ተወስኖ ሲገኝ ሲሆን በዚህ ሂደት ማህጸኑን በቀዶ ጥገና በማውጣት የመታከም እድል አለው፡፡

ካንሰሩ ከማሕጸን ጫፍ ከዘለለ በኋላ ግን ቫይረሱ ወደ ሌሎች የሰውነት አካል የመዛመት እድሉን ስለሚያፋጥን ከባድ ይሆናል ይላሉ፡፡

ቫይረሱ ከማህጸን አልፎ ወደ ሌሎች ቦታዎች መዛመት ከጀመረ በኋላ የሚሰጠው ህክምና በጨረርና በኬሞቴራፒ ማከም እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version