ዓለምአቀፋዊ ዜና

እስራኤል በጋዛ በየቀኑ የአራት ሰዓታት የተኩስ አቁም ልታደርግ ነው

By Melaku Gedif

November 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በየቀኑ የአራት ሰዓታት የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማቷን አሜሪካ አስታውቃለች፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተኩስ አቁሙ ትክክለኛ እና በቀጣናው የሚፈለገውን መሻሻል ለማምጣት ሚናው ከፍተኛ ነው ሲሉ አወድሰዋል፡፡

የተሰኩስ አቁሙ በዋናነት በሥፍራው የሚገኙ ንጹሃን ዜጎችን ከአካባቢው እንዲሸሱ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ከዚህ ባለፈም በቦታው ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረሰ እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡

የእስራኤል ጦር ከዚህ በፊት በጋዛ ለሚኖሩ ንጹሃን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ “ታክቲካል የተኩስ አቁም” እንደሚያደርግ ማስታወቁን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡

በእስራኤል እና ሃማስ መካከል እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት በጋዛ ሆስፒታሎችን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች እየወደሙ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

እስካሁንም በጋዛ 11 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ለህልፈት ሲዳረጉ÷ በርካቶች ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።