የሀገር ውስጥ ዜና

የሲሚንቶና የብረት ዋጋ ቅናሽ ማሳየቱ ተመለከተ

By Amele Demsew

November 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲሚንቶ፣ በብረትና ሌሎች የግንባታ እቃዎች ላይ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችና ነጋዴዎች ገለጹ፡፡

ፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት በተለያዩ የሲሚንቶና የብረት ማምረቻ ፋብሪካዎችና የንግድ ሱቆች ላይ ተዘዋውሮ ምልከታ አድርጓል፡፡

በተደረገው ምልከታም የ1 ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ ከ800 ብር እስከ 500 ብር ቅናሽ እንዲሁም 1 ቤርጋ ፌሮ በኪሎ የ15 ብር ቅናሽ ማሳየቱን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የሲሚኒቶና ብረት ግብይት በሚደረግባቸው አካባቢዎች በተደረገው ምልከታም የሲሚኒቶ፣ የብረት እና ሌሎች የኮንስትራክሽን እቃዎች ቅናሽ ማሳየታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ቀደም ሲል ግብይቱ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተመን ወጥቶለት ሲሸጥ የቆየ ቢሆንም ከታህሳስ ወር 2015 ዓ.ም ወዲህ ግን በነጻ ገበያ መርህ ፋብሪካዎች ባቀረቡት ዋጋ ግብይትት መካሄድ መቀጠሉን በቅኝቱ ወቅት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ሲሚንቶ ከ1 ሺህ 800 እስከ 2 ሺህ ሲሸጥ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ኢትዮ ሲሚንቶ ከ1 ሺህ 250 እስከ 1 ሺህ 270፣ ሀበሻ ሲሚንቶ በ1 ሺህ 300 ብር እና ሙገር ሲሚንቶ በ1 ሺህ 350 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል÷ የብረት ገበያም በተመሳሳይ ምልከታ የተደረገበት ሲሆን በተመሳሳይ ቅናሽ የታየበት መሆኑን ለመመልከት ተችሏል፡፡

ለአብነትም 10 ቤርጋ ብረት 1 ሺህ 332 ሲሸጥ የቆየ ሲሆን አሁን ላይ 1 ሺህ 36 ብር፣ 14 ቤርጋ ፌሮ ብረት 3 ሺህ 412 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን አሁን 2 ሺህ 654 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡

በዘርፉ ላይ የተሰማሩት አምራቾችና ነጋዴዎች ሲሚንቶ፣ ብረትና ሌሎችም የግንባታ እቃዎች ሸማቾች ቁጥር መቀነሱንም አመላክተዋል።

በሜሮን ሙሉጌታ