የሀገር ውስጥ ዜና

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ለአረጋውያን ማዕከል ግንባታ ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች

By Melaku Gedif

November 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አምባሳደር ሙሐመድ ሳሊም አል ራሺዲ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ ለአረጋውያን የሕክምና፣ የገቢ ማስገኛ እና ሁለገብ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ለአምባሳደሩ አብራርተዋል፡፡

ደረጃውን የጠበቀ የአረጋውያን ማዕከል ለመገንባት የዲዛይን ስራ ተጠናቅቆ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመው÷ ለግንባታውም የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል።

አምባሳደር ሙሐመድ ሳሊም አል ራሺዲ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት በብሔራዊ ደረጃ ለሚያስገነባው የአረጋውያን ማዕከል ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ አረጋውያንን ጨምሮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሕይወት ለመለወጥና ለማሻሻል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትንም አምባሳደሩ አድንቀዋል።