አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳይበር ጥቃት÷ ወደ ኮምፒውተር ሥርዓት በአውታረ-መረብ አማካኝነት በመግባት መረጃዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ተፈጸመ የምንለው ክስተት ነው፡፡
የሳይበር ጥቃቶች÷ ባልተገባ መንገድ በበይነ-መረብ ሥርዓት ውስጥ በመግባት ፋይል የሚያጠፉ፣ የሚሠርቁ ወይም ግላዊ መረጃዎችን ላልተገባ ዓላማ የሚያውሉ እና የሚያሠራጩ ሁኔታዎችንም ጭምር ያጠቃልላሉ፡፡
ጥቃት ፈጻሚዎቹ÷ ለዘመናት የተለፋባቸውን እጅግ አሥፈላጊ ሀገራዊ፣ ተቋማዊ እና ግላዊ ጥብቅ መረጃዎችና አገልግሎቶችን ከጥቅም ውጪ ሊያደርጓቸው ይችላሉ፡፡
የሳይበር ደኅንነት ጥንቃቄ ካልተደረገ÷ ፋይሎች ሊሰረዙ ወይም ጥቃት ፈጻሚዎቹ አባዝተዋቸው ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ አገልግሎት ላይ ሊያውሏቸው ይችላሉ፡፡
የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚከተሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎች ይተግብሩ ÷
1. ሁል ጊዜ ተገቢውን የሳይበር ደኅንነት ጥንቃቄ ያድርጉ፣
2. ጸረ-ቫይረስ ሶፍትዌሮችን ማሻሻልና ሶፍትዌሮችን በየጊዜው ማዘመን አይዘንጉ፣
3. የተለያዩ የጥቃት ሙከራዎች ሲያጋጥምዎ ለባለሙያ ማሳወቅ አይርሱ፣
4. ምናልባት ፋይልዎ ቢጠፋ መልሰው መተካት ይችሉ ዘንድ መጠባበቂያ ፋይሎችን መያዝ አይዘንጉ፣
5. አጠራጣሪ አድራሻ ወይም ኢሜል በሥህተት ከከፈትን በቶሎ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ማሳወቅ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር ዕድል ስለሚፈጥር ሁኔታውን ከማሳወቅ ችላ አይበሉ፣
6. በመጨረሻም በሳይበር ደኅንነት ላይ ግንዛቤ ማሳደግ፣ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲዎችን እና ሕጎችን ማንበብ ለሳይበር ጥቃት ያለንን ተጋላጭነት ለመቀነስ ዓይነተኛ መሆናቸውንም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር መረጃ ያመለክታል፡፡