ዓለምአቀፋዊ ዜና

በጋዛ ሰብዓዊ አቅርቦት ለማሳለጥ ጦርነቱ ጋብ እንዲል የቡድን 7 አባል ሀገራት ጠየቁ

By Alemayehu Geremew

November 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰብዓዊ አቅርቦት ለማሳለጥ እስራዔል ጋዛ ላይ የምትፈጽመውን የቦምብ ድብደባ ጋብ እንድታደርግ የቡድን 7 አባል ሀገራት ጠየቁ፡፡

የየሀገራቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በጋዛ ሠርጥ ዕርዳታ ለንጹሐን ማድረስ ይቻል ዘንድ “ሰብአዊ ተኩስ አቁም” እንዲደረግ መጠየቃቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

እንደ አልጀዚራ መረጃ ከሆነ አሁን ላይ የቡድኑ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለአንድ ወገን ያደላ ከሚመስል ውሳኔ ወጥተው በጋዛ ለሚገኙ ንጹሐን ሕይወት ግድ ይላቸው ጀምሯል፡፡

በቶኪዮ ባደረጉት ጥልቅ ሥብሰባም በእስራዔል – ሃማስ ጦርነት ላይ አንድ አቋም መያዝ መቻላቸውን ዘገባው የሚያመላክተው።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ÷ እንደ ምግብ ፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፣ የሕክምና አገልግሎት እና መጠለያ የመሠሉ አቅርቦቶች ለንጹሐን መድረሳቸውን ማረጋገጥ ያሥፈልጋል ብለዋል፡፡

የብሪታንያ ፣ ካናዳ ፣ ፈረንሳይ ፣ ጀርመን ፣ ጃፓን እና ጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም፥ የተባሉትን መሰረታዊ አቅርቦቶች እና አስቸኳይ ዕርዳታዎች ለማድረስ “ሰብአዊ ተኩስ አቁም” ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ንጹሐን በነጻነት መንቀሳቀስ ታጋቾችም መለቀቅ እንዳለባቸውም ሚኒስትሮቹ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የእስራኤል ሃማስን ጦርነት ተከትሎ እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።