ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሩሲያ የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኛ ላይ የእሥር ትዕዛዝ አወጣች

By Alemayehu Geremew

November 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ላይ የመያዣ ትዕዛዝ እንዲወጣባቸው ውሳኔ ባስተላለፉት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኛ ላይ የእሥር ትዕዛዝ አወጣች፡፡

ዳኛው ባሳለፍነው የፈረንጆቹ መጋቢት ወር በፕሬዚዳንት ፑቲን ላይ የጦር ወንጀል ክሥ ማቅረባቸውን ታስ የተሰኘው ግዙፍ የሩሲያ የዜና ምንጭ አስታውሷል፡፡

እንደ ዜና ምንጩ መረጃ ከሆነ ሰርጂዮ ጄራርዶ ኡጋልዴ ጎዲኔዝ የተባሉት የዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኛ÷ ከዛሬዋ ዕለት ጀምሮ ሥማቸው በ”ይፈለጋል” ዝርዝር ውስጥ ሰፍሯል፡፡

ዳኛው በሩሲያ የ’ይፈለጋሉ’ ዝርዝር ውስጥ ሲገቡ ሁለተኛው የተቋሙ ሰው ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በዓለም ዓቀፍ ፍርድቤቱ ዐቃቤ ሕግ ካሪም ካን ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣቷን ዘገባው አስታውሷል።

ይህም በሩሲያ ፌዴሬሽን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፅ መሠረት እንደሆነና ሥማቸውም በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የመረጃ ቋት ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኝ ሬዲዮ ፍሪ ይሮፕ የተሠኘው የዜና ምንጭ አስነብቧል፡፡

ዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን እና በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኮሚሽነር ማሪያ ልቮቮ-ቤሎቫ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን በሕገ-ወጥ መንገድ ከዩክሬን አስኮብልለዋል በሚል ክሥ የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣቱን ተከትሎ በበኩሏ የእሥር ትዕዛዝ አውጥታለች፡፡