አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የምታደርገውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት የዳታ ማዕከላትን የማስፋት እና የማጠናከር ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የዳታ ማዕከላትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ለፋይናንስ ሴክተርና ለቴክኖሎጂ እድገት ለማዋል ያለመ የውይይት መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግሩን የሚያግዙ የተለያዩ የዳታ ማዕከላትን ወደ ስራ ማስገባቷን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ዊንጉ አፍሪካ የተሰኘ የግል ዘርፍ በማሳተፍ በአይሲቲ ፓርክ ውስጥ ኢንቨስት ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በዚሁ ረገድ የግሉን ዘርፍ ጭምር በማሳተፍ የተጠናከረና ደህንነቱ የተጠበቀ የዳታ ማዕከል ልማት ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በዘርፉ ስራ የጀመረው ዊንጉ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተሾመ ወርቁ÷ የዲጂታል ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማገዝና ሀገሪቱ በቀጣናው ያላትን የዲጂታል ትስስር መሪነት ለማጠናከር ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ ሄኖክ አህመድ በበኩላቸው÷ አይሲቲ ፓርክ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከድህነት ለመውጣት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የዳታ ማዕከል እንዲሆንና ሚናውን እንዲወጣ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሳሙኤል ወርቃየሁ እና ዘረአያዕቆብ ያዕቆብ