አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን በዛሬው እለት ሁለት የቴሌኮሙኒኬሽን ፈቃዶችን ለመስጠት የፍላጎት መግለጫ መጠየቂያ አውጥቷል።
ባለሥልጣኑ የፈቃድ አሠጣጥ ሂደቱን በኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ በተሠጠው ሥልጣን መሠረት እየመራ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያን የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ለግሉ ዘርፍ የመክፈት ሂደት ዋናው አካል መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንክኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ይዞ ከሚገኘው ፈቃድ በተጨማሪ ሁለት ፈቃዶችን በቴሌኮሙኒኬሽን ሥራ ላይ ለተሠማሩ ኩባንያዎች የመሥጠት ሂደት መንግስት በዘርፉ ውድድርን ለመፍጠር ካቀዳቸው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑንም ጠቅሷል።
በዚህም የመንግስት ዋና ዋና ዓላማዎች የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን ተደራሽነትና ቀልጣፋነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚውን ለውጥ ለማፋጠን የሚያስፈልገውን የአገልግሎት ጥራትና ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እና ከዲጂታል ኢኮኖሚ የሚገኘውን ጥቅም የበለጠ ለማስፋት መሆኑንም ባለስልጣኑ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ሁለት ሀገር አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ ፈቃዶች መስፈርቶችን ለሚያሟሉ የቴሌኮሙኒኬሽ ኩባንያዎች በኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011 መሠረት በውድድር ላይ በተመሠረት ግልፅ ጨረታ የሚሰጡ ይሆናል መሆኑን ጠቅሷል።
ማንኛውም ፍላጎት ያለው ኩባንያ የፍላጎት መግለጫውን እስከ ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት ድረስ እንዲስገባ የተጋበዘ ሲሆን ስለፍላጎት መግለጫው ዝርዝር መመሪያ በባለስልጣኑ ድረ-ገጽ (www.eca.et) ላይ ማግኘት የሚቻል መሆኑ አስታውቋል።
ባለስልጣኑ በማከልም ይህ የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍን ለግሉ ዘርፉ የመክፈት ሂደት እየተካሄደ ያለው በአለማችን እንዲሁም በኢትዮጵያ ተከስቶ ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ሲሆን ይህም መንግስት ወረርሽኙን በጥንካሬ እየተዋጋ ጎን ለጎን የተጀመሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን የማስቀጠል ቁርጠኝነትን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሷል።
የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ ለመክፈት እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ሊመጣ የሚችለው ለውጥ ለማስቀጠል መንግስት ያለው ቁርጠኝነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጿል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።