አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 27 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም ሰው የኢንተርኔት ዓለም እውነታዎችን መረዳት እና ማወቅ አለበት፡፡
በኦንላይ የሚደረጉ ግብይቶች፣ የመረጃ ልውውጦች እና የምናጋራቸው መረጃዎች እንዴት በእውነተኛ ህይወት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ማወቅ እና መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
በኦንላይን ከምናጋራውም ሆነ ከምንከፍተው ሊንክ (ማስፈንጠሪያ) መጠበቅ የግላችንን ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው።
ከሰሞኑ በርካታ የቴሌግራም እና ፌስቡክ አካውንቶች ላይ እውነት የሚመስሉ ነገር ግን ከጀርባቸው አንዳች ነገር የያዙ ሊንኮች ወይም መልዕክቶች ሲዘዋወሩ ይስተዋላል።
የእነዚህ ሊንክ ፈጣሪዎች ግላዊ መረጃ ለመውሰድ በማሰብ እጅግ አሳማኝ እና ትክክል የሚመስሉ መረጃዎችን በማጋራት ሊንኩ ሲከፈት ሙሉ ስም፣ የቤት አድራሻ እና ስልክ ቁጥር በመጠየቅ ስለግለሰቡ መረጃ ካገኙ በኋላ ለቀጣይ ጥቃት የሚዘጋጁባቸው መንገዶች ናቸው፡፡
ብዙ የግል መረጃዎችን በኦንላይን ማጋራት አጭበርባሪዎች ከፈጠሩት አጀንዳ አሳሳችነት አንጻር አንዳንድ ጊዜ ከመጠን በላይ ራስን ማጋለጥ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
በኦንላይን መረጃ ከመስጠትዎ በፊት የተቀባዩን ማንነት እና ትክክለኛነት ማረጋገጥ የግድ ያስፈልጋል፡፡
ግላዊ መረጃ በጥቁር ገበያ ስለሚሸጥ እና ብዙ ዋጋ ስለሚያወጣ የሳይበር ወንጀለኞች የመረጃ ግላዊነትን ይጥሳሉ።
ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰረቀ መረጃ በጥቁር ገበያ በተለያዩ ሃገራት የሚገኝ ሲሆን በሀገራችንም የሳይበር ወንጀለኞች በኦንላይን መረጃዎችን እንደሚሸጡየኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የላከው መረጃ ያመላክታል።
በሀገራችን የሳይበር ወንጀለኞች በኦንላይን የሚሸጧቸው የመረጃ አይነቶችም፥
የሞባይል ስልክ ቁጥሮች፣ የኢሜይል አድራሻዎች፣ የክሬዲት/ATM ካርድ/ባንክ አካውንት ቁጥሮች፣ የIP አድራሻዎች፣ የይለፍ ቃል ወይም PIN Code እና ሌሎች የግል መረጃዎችን ነው።
ህብረተሰቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ግላዊ መረጃዎችን ከአጭበርባሪዎች እንዲጠብቅ አስተዳደሩ አስገንዝቧል።