የሀገር ውስጥ ዜና

የቡድን 7 አባል ሀገራት በጋዛ እና በዩክሬን ጉዳይ ቶኪዮ ላይ ሊመክሩ ነው

By Alemayehu Geremew

November 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡድን 7 አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቶኪዮ ላይ ተገናኝተው በጋዛ እና በዩክሬን ጉዳይ ሊመክሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ዛሬ እና ነገ የሚካሄደውን ስብሰባ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮኮ ካሚካዋ ይመሩታል ተብሏል፡፡

ካሚካዋ አስቀድመው የእስራዔል ፣ ፍልሥጤም እና ዮርዳኖስ አቻዎቻቸውን ለማግኘት በሀገራቱ የሥራ ጉብኝት አድርገው ሰሞኑን እንደተመለሱ መኽር የተሰኘው የዜና ምንጭ አስነብቧል፡፡

ሀገራቱ ከውይይታቸው በኋላ የጋራ የአቋም መግለጫ ያውጡ አያውጡ እስከ አሁን የታወቀ ነገር የለም ነው የተባለው።

ዲፕሎማቱ በሕንድ-ፓሲፊክ ቀጣና ስላለው ሁኔታ እንዲሁም ለዩክሬን ስላላቸው የማይታጠፍ ድጋፍ እንደሚወያዩም ተጠቁሟል፡፡

የመካከለኛው እስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የዩክሬኑ ከፍተኛ ዲፕሎማት ዲሚትሪ ኩሌባ በውይይቱ እንደሚካፈሉ ይጠበቃል፡፡